የኦጋዴኑ ጀግና – ደጃዝማች ነሲቡ ዘአማኑኤልና የቴዲ አፍሮ አዲስ አልበም ፖስተር

አቻምየለህ ታምሩ

መስከረም 22 ቀን 1928 ዓ.ም. ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የፋሽስት ጥሊያንን ወረራ ለመመከት የክተት አዋጅ ካስነገሩ በኋላ የኢትዮጵያን ጦር በተለያዩ ግንባሮች እንዲመሩ ለጦር አበጋዞቻቸው ስምሪት ሰጥተው ነበር። በምስራቅ በኩል ወረራ የፈጸመውን ማርሻል ሩዶልፎ ግራኒያኒን ለመውጋት ወደ ደቡብ የዘመተው የኢትዮጵያ ጦር በሶስት ምድብ የተደራጀ ነበር። ሶስቱ ምድቦች ቀኝ ደቡብ፣ መሀል ደቡብና ግራ ደቡብ ይባላሉ።

የቀኙ የደቡብ የጦር ሰራዊት ዋና አዛዥ የወቅቱ የሐረር እንደራሴ የነበሩት ደጃዝማች ነሲቡ ዘአማኑኤል ነበሩ። በዋና አዛዡ በደጃዝማች ነሲቡ ዘአማኑኤል ስር የተመደቡት አዝማቾች ደግሞ ደጃዝማች ሃብተሚካኤል ይናዱ [የኩሎ ገዥ]፤ ደጃዝማች መኮንን እንዳልካቸው [የኢሊባቡር ገዥ]፤ ደጃዝማች አበበ ዳምጠው [የጎፋ ገዥ]፤ ደጃዝማች አምደሚካኤል ሃብተስላሴና የቆራሄው ጀግና ግራዝማች አፈወርቅ ወልደ ሰማዕት ናቸው።

የግራ ደቡብ የጦር ሰራዊት ዋና አዛዥ የወቅቱ የሲዳሞ ጠቅላይ ግዛት ዋና ገዢ ራስ ደስታ ዳምጠው ሲሆኑ በስራቸው የተመደቡት ደግሞ የአገር ግዛት ሚንስትሩ ደጃዝማች ገብረማርያም ጋሪ፤ የወላይታ ገዥው ደጃዝማች መኮንን ወሰኔ፤ ደጃዝማች ደባይ ወልደ አማኑኤልና ፊታውራሪ ታደሰ ገነሜ ነበሩ።

ሶስተኛው የደቡብ ምድብ የማህል ደቡብ ጦር ሲሆን የጦር ሰራዊት ዋና አዛዥ የወቅቱ የባሌ ጠቅላ ግዛት ገዢ ደጃዝማች በየነ መርዕድ ነበሩ። በደጃዝማች በየነ መርዕድ ስር የገንዘብ ሚንስትሩ በጅሮንድ ፍቅረስላሴ ከተማ፤ የጉማይ ጦር መሪው ፊታውራሪ አጥናፍሰገድ ወልደጊዮርጊስና ቀኛዝማች አስፋው ወልደጊዮርጊስ ሲሆኑን ኤርትራ ከነበረው የፋሽስት ጥሊያን ጦር ከድተው ለአገራቸው ለመዋጋት ከገቡት መካከል ቀኛዝማች ሰለባና የደርጉ የመጀመሪያ ሊቀመንበርና የኢትዮጵያ ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግስት ፕሬዝደንት የነበሩት የጀኔራል አማን ሚካኤል አንዶም አባት ቀኛዝማች አንዶም ይገኙበታል።

ደጃዝማች ነሲቡ ዘአማኑኤል የዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት ተማሪና በኢትዮጵያ ዘመናዊ ትምህርት ታሪክ ውስጥ ምዕራባዊ ወይንም አውሮፓዊ ትምህርት ከቀሰሙት ግንባር ቀደምቶች መካከል ሲሆኑ የአዲስ አበባ መዘጋጃ ቤት ኃላፊ ሳሉ ተራማጅ ተግባራትን እንደከወኑ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ “Pioneers Of Change In Ethiopia: Reformist Intellectuals Of Early Twentieth Century” በሚለው መጸሀፋቸው የደጃዝማች ነሲቡን ተራማጅ እርምጃዎች እንዲህ ይገልጧቸዋል፤

“the registration and categorization of urban land, the institution of traffic police and sanitation guards, a ban on the custom of firing shots during festivities, the proscription of the capricious system of leba shay, the burying of the bodies of dead animals, road-building, granting loans to people building houses along the main roads so that the construction would add to the beauty of the city, the institution of night guards to curb mugging and the municipal certification of contracts.”

በደቡብ ግንባር ከዘመተው የኢትዮጵያ ጦር መካከል በደጃዝማች ነሲቡ ዘአማኑኤል እንደሚመራር የቀኙ ደቡብ ጦር በፋሽስት ጥሊያን ላይ ተደጋጋሚ ድል ያስመዘገበ ምድብ የለም። በደጃዝማች ነሲቡ ዘአማኑኤል ስር ቆራሄ ላይ የመሸጉት ጀግናው ግራዝማች አፈወርቅ ወልደ ሰማዕት የወራሪውን የእግረኛ ጦር በተደጋጋሚ ድል መተዋል። በእግረኛ ጦር ሽንፈት የተከናነበው የግራዚያኒ ጦር የግራዝማች አፈወርቅን ሰፈር በአውሮፕላን መደብደብ ጀመረ። ሀያ ቦንም ጣይ አውሮፕላኖችርን አሰማርቶ ቀንና ሌሊት ሙሉ ቆራሄን በመርዝ ቦንብ ሲያጠፋ ዋለ። እግራቸው በአውሮፕላን ቦንብ የተመታው ግራዝማች አፈወርቅ ክፉኛ ቆሰሉ። የግራዝማች አፈወርቅን በጽኑ መቁሰልና ክፉኛ መታመም የሰሙት ደጃዝማች ነሲቡ ዘአማኑኤል ወደ ደጋሃቡር በአስቸኳይ ሄደው እንዲታከሙ ትዕዛዝ በመስጠት ግራዝማች አፈወርቅን ተክተው ጦር እንዲመሩ ፊታውራሪ ጓንጉል ኮሳሴ ሾሙ።

በእግረኛና በታንክ ድል ተነስተው የነበሩት ጥሊያኖች በአየር ድብደባው የግራዝማች አፈወርቅን በጽኑ መቁሰልና ወደ ደጋሃቡር መሄድ ሲሰሙ በካሚዮኖች እየሆኑ ብዙ ታንክ ይዘው በእግረኛና በታንክ ወደተሸነፉበት ወደ ቆራሄና ሐነለይ ሲገቡ አድፍጦ ይጠባበቅ የነበረው የፊታውራሪ ጓንጉል ኮሳሴ ጦር ጥቃት ሰንዝሮ አንድ ሳይቀር እብሪተኛውን የጥሊያን ጦር ደመሰሰ። በዚህ ድል የኢትዮጵያ ጦር በርካታ መትረየሶች፣ ጠመጃዎችና ጥይቶች ከጥሊያኖች ሊማርክ ችላል። በዚህ የተበሳጨው ፋሽስት ጥሊያን እንደገና ቦንብ ጣይ አውሮፕላኖችን በማሰማራት የኢትዮጵያን ጦርና ሰላማዊ ኢትዮጵያውያንን መጨፍጨፍ ጀመረ።

በመርዝ ጋር በተፈጸመው የአውርፕላን ድብደባ ብዙ ሰላማዊ ሰውና በርካታ አገሩን ለመከላከል ወደ ጦር ግንባር የወረደው መደበኛ ጦርና መደበኛ ያልሆነ ሰራዊት ለአገሩ ሉዓላዊነት መስዕዋት ሆነ። ማርሻል ግራዚያኒ በደጃዝማች ነሲቡ ይመራ የነበረውን የቀኙን የደቡብ ጦር ለበቀል ባካሄደው የአውርፕላን ድብደባ 15,000 ኢትዮጵያውያንን ገድሎ ኦጋዴንን ባጠቃላይ ተቆጣጠረ። በመጨረሻ ላይ በደጃዝማች ነሲቡ ይመራ የነበረው ቀኙ የደቡብ ጦር ተፈታ። መሪው ደጃዝማች ነሲቡ ዘአማኑኤልም ወደ ሐረር አፈግፍገው ድሬደዋ በመሄድ ሊግ ኢፍ ኔሽንስ ቀርበው አቤት ለማለት ከንጉሰ ነገስቱ ጋር ወደ ጄኔቭ አመሩ። ስዊስ አገር እንደደረሱ ንጉሰ ነገስቱ ከእየሩሳሌም ጀኔቭ እስኪደርሱ ድረስ ለተወሰነ ጊዜ በሊግ ኦፌ ኔሽንስ የኢትዮጵያ ዴሊጌሽን መሪ በመሆን አገልግለዋል። የኢትዮጵያ ዴሌጎሽን መሪ ሆነው በቆዩበት ጊዜ የወቅቱ የሊግ ዞፍ ኔሽንስ ዋና ጸሐፊ የፈረንሳዩ ፒየር ላቫል በመራው የሊጉ ጉባኤ ላይ የሙሶሎኒ ጦር የሚጠቀመውን የተከለከለ የመርዝ ጋዝ እንዲያቆም በመማጸን፤ ራሳቸውም በመርዝ ጋዝ እንደተጠቁና ጤናቸው እንደተቃወሰ የሀኪም ማስረጃ ጭምር በማቅረብ ሁለት ጊዜ ሁለት ጸረ የተከለከለ መርዝ መጠቀም ሪዞሊስኖች በኢጣሊያ ላይ እንዲተላለፍ ቢማጸኑም ውድቅ ተደረገባቸው።

በመጨረሻም ቆራሄ ጦር ግንባር ሳሉ የጥሊያን አውሮፕላኖች በጣሉት መርዛማ ቦንብ ጭስ ተበክለው ስለነበር እዚያው ስዊዝ አገር በስደት በሚኖሩበት ህመማቸው ጸንቶ በተወለዱ በ43 ዓመታቸው ዳቮስ ውስጥ በሚገኝ አንድ ሆስፒታል ውስጥ እ.ኤ.አ. ጥቅምት 16 ቀን 1936 አ.ም. ህይወታቸው አልፏል::
ከሰሞኑ የቴዎድሮስ ካሳሁንን «ኢትዮጵያ» የሚለውን የዘፈን አልበም ስዕላዊ ማስታወቂያ ተከትሎ በተለቀቀው ማስታወቂያ ላይ ጋሻና ጦር ይዘው የሚታዩትን በእድሜ የገፉ አርበኛ «የኦጋዴኑ ጀግና ራስ ነሲቡ ዘአማኑኤል» ናቸው የሚሉ ሰዎች ተመልክተናል። ይህ ትክክል አይደለም። የኦጋዴኑ ጀግና ደጃዝማች ነሲቡ ዘአማኑኤል ከፍ ብሎ እንደተገለጠው የሞቱት ገና ጎልማሳ ሳሉ በ43 ዓመታቸው ነው። ኦጋዴንም የዘመቱት እንዲሁ ጎልማሳ ሆነው ነው። በቴዲ ማስታወቂያ ላይ የሚታዩት አርበኛ ግን ቢያንስ እድሜያቸው ከ65 ዓመታት በላይ የሚሆኑ በእድሜ ሸምገል ያሉ አዛውንት ናቸው።

በርግጥ በጎግል ምስል መፈለጊያ ላይ የእኒህ አዛውንት [ቴዲ ማስታወቂያ ላይ ያሉት] ፎቶ አስገብተን ስንፈልግ ጎግል «የራስ ነሲቡ» ፎቶ እንደሆነ ይናገራል። ይህ ስህተት ነው። ምስሉን ጎግል ላይ የጫነው ሰው ከምስሉ ጋር የተሳሳተ መረጃ አብሮ ጭኗል። በቴዲ የአዲስ ዘፈን ማስታወቂያ ላይ ያሉትን ጋሻና ጦር የያዙ አርበኛ «የራስ ነሲቡ ፎቶ ነው» በማለት ብዙ ሰው የተሳሳተው ከጎግል ምስል መፈለጊያ ባገኘው መረጃ ላይ ተመርኩዞ ይመስለኛል። ጎግል ምስል መፈለጊያ ላይ የሚታየው ስህተት ህይ ብቻ አይደለ። ፎቶውን «የራሱ ነሲቡ» ፎቶ ነው ይልና ሀተታው ላይ በአድዋ ጦርነት ስለተሳተፉ ጀግኖችና ስለ አድዋ ዝክር ያወራል። ይህም ሌላ ስህተት ነው። ከላይ እንደቀረበው ደጃዝማች ነሲቡ ዘአማኑኤል የሁለተኛው ዙር የጥሊያን ወረራና የኦጋዴን ግንባር መሪ እንጅ ድል ያደረግንበት የአድዋ ጦርነት ጀግና አልነበሩም።

የቴዲ ማስታወቂያ ፎቶ የአድዋው ጀግናና የዳግማዊ አጤ ምኒልክ የፍትህ ሚንስትር የነበሩት የአፈንጉሥ ነሲቡ መስቀሎ ፎቶም አይደለም። የአፈንጉሥ ነሲቡ መስቀሎን ፎቶ ከታች አትሜዋለሁ። አያይዤም የደጃዝማች ነሲቡ ዘአማኑኤልን የተለያዩ ፎቶዎች ለጥፌዋለሁ። ከተለጠፉት ፎቶዎች ማመሳከር እንደሚቻለው በቴዲ ማስታወቂያ ላይ የሚታየው የአዛውንት አርበኛ ፎቶ የደጃዝማች ነሲቡ ዘአማኑኤልም ሆነ የአፈንጉሥ ነሲቡ መስቀሎ አይደለም።

ነገሩ ወዲህ ነው። የቴዲ አዲስ ዘፈን ማስታወቂያ ላይ የወጡት ጦርና ጋሻ ይዘው የሚታዩት አዛውንት አርበኛ ስማቸው አልተመዘገበም። አዛውንቱ አርበኛ ፎቶ የተነሱት ደቡብ ከዘመተው የኢትዮጵያ ጦር ጋር አብሮ ወደ ደቡብ በሄደው H. V. Drees በተባለ የብሪታንያ የፎቶ ጋዜጠኛ ሲሆን ፎቶ ጋዜጠኛው የAmerican Press ለሚባል ድርጅት የፎቶ ጋዜጠኛ ነበር። ፎቶ ጋዜጠኛው ጦርና ጋሻ የያዙር አዛውንቱ አርበኛ ከፊት ሆነው ከሚታዩበት ምስል ስር ስለ ፎቶው የሚከተለው መግለጫ አስፍሯል፤

“Lords of the desert. Desert nobles chanting their war cry as they trek across the Ogaden desert for the front. They are part of the irregular forces of Ras Nasibu, commander of the southern army.”

ከዚህ የፎቶ ጋዜጠኛው መግለጫ እንደምንረዳው በቴዲ አዲስ ዘፈን ማስታወቂያ ላይ ጋሻና ጦር ይዘው የሚታዩት አዛውንት አርበኛ ደጃዝማች ነሱቡ ዘአማኑኤል ወይንም ራስ ነሲቡ አሊያም አፈንጉሥ ነሲቡ መስቀ ሳይሆኑ ስማቸው ያልተጠቀሰ ግን የራስ ነሲቡ ዘአማኑኤል መደበኛ ያልሆነው ጦር አካል የነበሩ ተዋጊ አርበኛ ናቸው።

ምንጮች፡-
1. ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ፤“ሕይወቴና የኢትዮጵያ እርምጃ”፤[፲፱፻፷፭ ዓ. ም.] ከገጽ 199 –203
2. ደጃዝማች ከበደ ተሰማ፤ “የታሪክ ማስታወሻ” [፲፱፻፷፩ ዓ.ም.]፤ከገጽ 126 –136
3. ዘውዴ ረታ፤ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት [፳፻፬ ዓ.ም.]፤ገጽ 213 – 220
4. American Press: October 21, 1935

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s