የህወኻት መንግስት በጌዴኦ ህዝብ ላይ እያካሄደ የሚገኘውን የኃይል እርምጃ አስመልክቶ፣ በውጭ ከሚኖሩ የጌዴኦ ተወላጆች ኮሚዩኒቲ በኩል የተላለፈ የአቋም መግለጫ

የኢህአዴግ/ህወኻት መንግስት በጌዴኦ ህዝብ ላይ እያካሄደ የሚገኘውን የኃይል እርምጃና የሠብዓዊ መብት ረገጣ አስመልክቶ፣ በውጭ የሚኖሩ የጌዴኦ ተወላጆች ኮሚዩኒቲ በኩል የተላለፈ የአቋም መግለጫ

1. የጌዴኦ ሕዝብ በዞኑ ከሚኖረው የህብረተሰብ ክፍል (ጉራጌ፣ሲልጤ፣አማራ፣ ወላይታ፣ኦሮሞ፣ሲዳማ…..ወዘተ) ጋር ተጋብቶና ተዋልዶ እንዲሁም በደም ተሳስሮ በአንድነት ለበርካታ ዓመታት የኖረ ሕዝብ ነው፡፡ የጌዴኦ ሕዝብ ለብዙ ሺህ ዓመታት በአንድ ቦታ ተወስኖ የሚኖር ከመሆኑም ባሻገር አጎራባች ከሆኑ ሕዝቦች ጋር በሠላምና በህብረት እየኖረ የሚገኝ ሕዝብ ነው፡፡ ጌዴኦ አሁን ከሚገኝበትና ከሚኖርበት አካባቢ ውጭ ወደ ሌሎች ህዝቦች የመኖሪያ ግዛት ዘልቆ በመግባት የመሬት፣ የከብት፣ የኃብትና የንብረት ዝርፊያ እንዲሁም የመሬት ወረራ በመፈጸም ወይም ጦርነት ውስጥ በመግባት የሚታወቅ ሕዝብ አይደለም፡፡

በጌዴኦ የይርጋጨፌ ኦርጋኒክ ቡና አምራቾች ዩኒዬንና በዲላ ከተማ ነዋሪ በሆኑ ውስን ነጋዴዎች መካከል ከኢንቨስትመንት ቦታ ጋር በተያያዘ በተነሳው የይገባኛል ክርክርና ወደ ፍርድ ቤት ባመራው ጉዳይ ላይ በመጀመሪያ በጌዴኦ ዞን ፍትህ ጽ/ቤት፣ በሁለተኛ ደረጃ በክልሉ መንግስት ፍትህ ቢሮ የኢንቨስትመንት ቦታው ለዩኒዬኑ እንዲሰጥ በመወሰኑ፣ የነጋዴው ቡድን የተላለፈውን ውሳኔ በመቃወም ጉዳዩ በፌዴራል ሠበር- ችሎት እንዲታይ ለሶስተኛ ጊዜ ሊያቀርብ ችሏል፡፡

የኢህአዴግ/ህወኻት መንግስት በጉዳዩ ላይ የመጨረሻ ውሳኔ ሳይሰጥ ለበርካታ ዓመታት በማጓተቱ፣ የጌዴኦ ሕዝብ ችግሩ በሠላማዊ መንገድ እንዲፈታ የተለያዩ ጥረቶችን ሲያደርግ የነበረ ቢሆንም፣ መንግስት ለጉዳዩ ልዩ ትኩረትና ክብደት በመስጠት የማያዳግም ውሳኔ ከመስጠት ይልቅ የህዝቡን ጥያቄ በንቀት ሲመለከተው ቆይቷል፡፡ ይህም ሥረዓቱ ለጌዴኦ ሕዝብ መልካምና ቀና የሆነ አመለካከት እንዴሌለው እንዲሁም ሕዝቡን በግልጽ እየበደለ ስለመሆኑ አመላከች ተግባር ነው፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢህአዴግ/ህወኻት መንግስት ከድንበር ማካለል ጋር ተያይዞም ይሁን በሌላ ምክንያት በህዝቦች መካከል የሚፈጠሩ አለመግባባቶችንና ግጭቶችን ለሚያካሂደው የብሔር ፖለቲካ አጀንዳና ፕሮፖጋንዳ መጠቀሚያነት ሲያውል የኖረ መንግስት በመሆኑ፣ ለበርካታ ዓመታት ውሳኔ ሳያገኝ የቆየውን ጉዳይ አገሪቱ በውስጥ የፖለቲካ አለመረጋጋት ቀውስ ውስጥ በምትገኝበት ጊዜ የፌዴራሉ ሠበር-ሰሚ ችሎት በየደረጃው የሚገኙ የፍትህ ተቋማት የሰጡትን የፍትህ ውሳኔ በመሻርና የአገሪቱን ህገ-መንግስት በተጻረረ መንገድ የኢንቨስትመንት ቦታው ለነጋዴው ቡድን እንዲሰጥ በመወሰን፣ በኣካባቢው ግጭት እንዲቀሰቀስ አድርጓል፡፡ መንግስት ግጭቱንም ለብሔር ተኮር ፖለቲካው ፕሮፖጋንዳ ማራመጃ ተጠቅሟል፣ እየተጠቀመም ይገኛል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ገዠው መንግስት በሚሰጠው የፖለቲካ አመራር ብቃት ማነስ፣ ነጻና ገለልተኛ የሆነ የፍትህ አስተዳደር ባለመዘርጋቱ፣ የኃላፊነትና የተጠያቂነት መርህ ባለመኖሩ፣ የተዛባ የፍትህ ውሳኔ አሰጣጥ በአገሪቱ በመንሰራፋቱና ሥርዓቱ በአጠቃላይ በሙስናና በመልካም አስተዳደር እጦት በመዝቀጡ ምክንያት የሚፈጠሩ ችግሮችን መንግስት አምኖ ከመቀበል ይልቅ፣ ለሃያ አምስት ዓመታት ችግሩን በህዝብ ላይ ሲያላክክ ኖሯል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ በጌዴኦ ዞን ለተፈጠረው ግጭት በመንግስት የፖለቲካ አመራር ውድቀትና በፍትህ አስተዳደሩ የተዘባ ፍርድ ምክንያት የተከሰተ ችግር እንደሆነ ከመቀበል ይልቅ፣ የኢህአዴግ/ህወኻት መንግስት የጌዴኦን ሕዝብ የግጭቱ ቀስቃሽና ተጠያቂ ከማድረጉም በላይ ሠላማዊና ታታሪ የሆነውን የጌዴኦ ሕዝብ እብሪተኛ፣ ወንጀለኛና ዘራፊ አድርጎ ፈርጇል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ መንግስት ግጭቱ በብሔሮችና በኃይማኖቶች ላይ ያነጣጠረ እንደሆነ በአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትርና ሌሎች ከፍተኛ ባለስልጣናት በኩል በተደረገ ጋዜጣዊ መግለጫ ተገልጿል፡፡

መንግስት ግጭቱን ለብሔር ፖለቲካ ማራማጃ ፕሮፖጋንዳ እየተጠቀመ የሚገኝ ቢሆንም፣ እኛ በውጭ የምንኖር የጌዴኦ ተወላጆች መንግስት በሕዝባችን ላይ የከፈተውን የስም ማጥፋት ዘመቻ እንዲሁም ለሚያራምደው የጎሳ ፖለቲካ ሕዝቡን መጠቀሚያ ማድረጉን በአስቸኳይ እንዲያቆም እንጠይቀለን!!!! ድርጊቱንም እንቃወማለን!!!!!! ለግጭቱ መቀስቀስ የሥረዓቱ የፖለቲካ አመራሩ የተፈጠረ መሆኑን እንገልጻለን!!!!!!

በአጠቃላይ በጌዴኦ ሕዝብና ለዘመናት በዞኑ ነዋሪ በሆነው ህብረተሰብ መካከል በተፈጠረው ግጭት ምክንያት በጠፋው ውድ የሰው ህይወትና በደረሠው የንብረት ውድመት በውጭ የምንኖር የብሔሩ ተወላጆች የተሰማንን ጥልቅ ኃዘን እንገልጻለን!!!!

2.መንግስት አገሪቱ በውስጥ የፖለቲካ አለመረጋጋት ችግር ውስጥ እንደምትገኝ በመግለጽ፣ በመላው አገሪቱ ያወጀውን የአስቸከኳይ ጊዜ አዋጅ ተከትሎ የጌዴኦ ዞንን በቀይ መስመር/ክልል ውስጥ በመመደብ በዲላ ከተማ፣ በስድስቱም ወረዳዎችና የወረዳ ከተሞች እንዲሁም ቀበሌዎች ውስጥ የጌዴኦ ታዋቂ በሆኑ ግለሰቦች፣ የህዝቡን የፖለቲካ፣የኢኮኖሚና ማህበራዊ መስተጋብር አስመልክቶ ጥናትና ምርምር የሚያደርጉ ምሁራን፣ በጡረታ የተገለሉ ሰዎች፣ ከፍተኛና መካከለኛ የሆኑ ባለኃብቶች፣ በቅርቡ ከዩኒቨርስቲ የተመረቁ ተማሪዎች፣ በመንግስትና በግል ሥራ ላይ

ተሰማርተው የሚገኙ የብሔሩ ልጆች፣ ሴቶች እንዲሁም ተማሪዎች ላይ በአጋዚ ሠራዊት የሚካሄደው ድብደባ፣ እስርና በስውር እየተካሄደ የሚገኘው ግድያ፣ በአስቸኳይ እንዲቆም እንጠይቃለን!!!! ድርጊቱንም እንቃወማለን!!!!!

3.በኢህዴግ/ህወኻት የፀጥታ ኃይሎች በዲላ ከተማና በስድስቱ የወረዳ ከተሞች ውስጥ በእስር ላይ የሚገኙ ወጣቶችን በምሽት በትላልቅ የጭነት መኪና በውል ወደማይታወቅ ሥፍራ የሚካሄደው የማጓጓዝ ተግባር፣ በአስቸኳይ ይቁም!!! በጉዳዩም ላይ ለወላጆች ግልጽ መረጃ እንዲሰጥ እንጠይቃለን!!!!!! ድርጊቱንም እናወግዛለን!!!!!!

  1. የኢህአዴግ/ህወኻት መንግሰት በጌዴኦ ሕዝብ ፖለቲካዊ፣ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ መስተጋብር ላይ ጥላሸት በመቀባት ሕዝቡን በማሸማቀቅ እያካሄደ የሚገኘውን የፕሮፖጋንዳ ሥራ እንዲሁም በጌዴኦ ሕዝብ ላይ እየተካሄደ የሚገኘውን የጅምላ ግድያ፣ እስራትና ድብደባ እንዲሁም የሠብዓዊ መብት ጥሰት በአስቸኳይ እንዲቆም እንጠይቃለን!!!! ድርጊቱንም እንቃወማለን!!!!
  2. የጌዴኦ ሕዝብ ከሚያመርተው የቡናና ሌሎች የግብርና ምርት ውጤት ውስጥ ቀጥተኛ የኢኮኖሚው ተጠቃሚ እንዲሆን ከፍተኛ እንቅስቃሴ

ያደርጉ የነበሩትንና በአርሶ አደሩ ስም የተቋቋሙ ማህበራትን የኢህአዴግ/ህወኻት መንግስት በስውር ባደረጃቸው ወንጀለኛ አስመጪና ላኪ የንግድ ድርጅቶች አማካይነት በቢሊዮን የሚገመት የኢትዮጵያ ብር በደረቅ ቼክ የማጭበርበር ወንጀል ተፈጽሞባቸዋል፡፡ በዚህ ምክንያት ማህበራቱ ለከፋ ኪሣራ ተዳርገዋል፣ በሂደት ከነበሩበት የቡና ገበያ ውድድር ውጭ እንዲሆኑ ተደርገዋል፡፡

 

የጌዴኦ ሕዝብ የህወኻት አመራሮች ባደራጇቸው ስውር የወንጀል ተቋማት የተፈጸመበትን ወንጀልና የደረሰበትን የፋይናንስ ኪሣራ ተቋቁሞ፣ የ ይርጋጨፌ ቡና አምራቾች ዩኒዬንን አቋቁሞ ዳግም በንግድ እንቅስቃሴ ውስጥ መሳተፍ መጀመሩን ተከትሎ፣የኢህአዴግ/ህወኻት መንግስትና በአካባቢው እንዲሁም ከዞኑ ውጭ የሚገኙ አንዳንድ ባለኃብቶች የዩኒዬኑን የፋይናንስ አቅም ዳግመኛ ለማሽመድመድ በስውር እየተንቀሳቀሱ እንደሆነ ለመገንዘብ ተችሏል፡፡

በመሆኑም የኢህአዴግ/ህወኻትም ሆነ በዞኑ የምትገኙ ባለኃብቶች የጌዴኦ ሕዝብና የይርጋጨፌ ኦርጋኒክ ቡና አምራቾች ዩኒዬን የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ መሆኑን ተገንዝባችሁ፣ ዩኒዬኑን በማፍረስ የህዝቡን የኢኮኖሚ መሠረት ለመናድ የምታካሂዱትን የጥፋት እንቅስቃሴ በአስቸኳይ እናወግዛለን!!!! እንድታቆሙ እንጠይቃለን!!!!! ድርጊቱንም አጥብቀን

6. የጌዴኦ ሕዝብ አገሪቱ ለዘመናት በኤክስፖርት ምርት ለዓለም ዓቀፉ የገበያ ማዕከል የምታቀርበውንና ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ገቢ የሚያስገኘውን የይርጋጨፌ ስፔሻላይዝድ (Specialized) ኦርጋኒክ ቡና እንዲሁም ሌሎች የግብርና ውጤቶችን አምራች ሲሆን፣ በዚህም ዞኑ ከአገሪቱ ጥቅል ዓመታዊ ምርት ወይም Gross Domestic Product /GDP/ ውስጥ ከ20-30% በመቶ የሚሆነውን ምርት አምራችና በአገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ውስጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሲያበረከት የኖረ እና እያበረከተ የሚገኝ ሕዝብ ቢሆንም፣ሕዝቡ በአፄዎቹና በደርግ ሥረዓት እንዲሁም በኢህአዴግ/ህወኻት የሃያ አምስት ዓመት አገዛዝ ውስጥ ተገፍቶና ተጨቁኖ እየኖረ ይገኛል፡፡

በመሆኑም የጌዴኦ ሕዝብ ለአገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ከሚያበረክተው አስተዋጽኦ አንጻር፣ በአገሪቱ የፖለቲካ ምህዳር ውስጥ ያለው የውሳኔ ሰጪነት ሚና እንዲረጋገጥ፣ በአካባቢው የመልማት መብቱ እንዲከበር፣ እራሱን በራሱ የማስተዳደደር መብቱ እንዲጠበቅና አሁን ዞኑን በማስተዳደር ላይ የሚገኘው ወታደራዊ ኃይል ከዞኖ በአስቸኳይ እንዲወጣ፣ በጌዴኦ ማንነት ላይ እየተቃጣ የሚገኘው ጥቃት በአስቸኳይ እንዲቆም፣ በሕዝቡ ላይ በህቡዕ የሚካሄደው ጥቃት በአስቸኳይ እንዲቆምና ከአገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ውስጥ ዕኩል ተጠቃሚ እንዲሆን እንጠይቃለን!!!!!!

  1. በዞኑ ከፍተኛ የሆነ ቀውስ ቢፈጠርም፣ መንግስት ምንም ዓይነት ችግር እንዳልተከሰተና እንዳልተፈጠረ በማስመሰል በኮማንድ ፖስቱ የሚመራው ኃይል ሕዝቡን በማፈን ውስጥ ለውስጥ ከፍተኛ የጅምላ እስር፣ ድብዳባ እና ግድያ እየፈጸመ ይገኛል፡፡ ሆኖም ጉዳዩን አስመልክቶ የመንግስት እንዲሁም የግል የመገናኛ ብዙኃን ሚዲያ ተቋማት ካላቸው ሙያዊ ኃላፊነት አንጻር የኮማንድ ፖስቱ ልዩ ኃይል በሕዝቡ ላይ እየወሰደ የሚገኘውን ጥቃት አስመልክቶ ሚዛናዊ የሆነ መረጃ አላስተላለፉም፡፡ ስለሆነም በጌዴኦ ሕዝብ ላይ ልዩ ኃይሉ እየፈጸመ የሚገኘውን የጭካኔ እርምጃ ሙያዊ ሥነ- መግባራችሁ በሚፈቅደው መሠረት ለዓለም ሕዝብ እንድታጋልጡ እንጠይቃለን!!!!!
  2. በኢህአዴግ/ህወኻት ልዩ የአጋዚ የጸጥታ ኃይል በንፁሃን የጌዴኦ ተወላጆች በተለይም ዕድሜያቸው ከአስራ ስምንት ዓመት በታች በሆኑ ልጆች ላይ በወሰደው እርምጃ በመቶዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች፣ሴቶችና ሕጻናትን በአደባባይ ገድሏል፡፡ በመቶዎች የሚቆጠሩ ግለሰቦች ላይ ከፍተኛ የአካል ጉዳት አድርሰዋል፡፡ ስለሆነም ገዳዮቹና የሠብዓዊ መብት ጥስት የፈጸሙ የፀጥታ ኃይሎች በአስቸኳይ ለፍርድ እንዲቀርቡ እንጥይቃለን!!!!!

9. የኢህአዴግ/ህወኻት መንግስት በጌዴኦ ዞን በተለያዩ ጊዜያት እየተፈጠረ ለሚገኘው ግጭትና ለግጭቱ መከሠት መንስዔ የሆነውን ችግር ከሥር መሠረቱ ፈትሾ ዘላቂ ሠላም ማስፈን በፍጹም አይፈልግም፡፡ ምክንያቱም በሕዝቦች መካከል የሚፈጠሩ ግጭቶችን ለሚያካሂደው የብሔር ፖለቲካ ፕሮፖጋንዳ መጠቀሚያነት እንዲሁም ለሥርዓቱ የስልጣን ዘመን ማራዘሚያነት እየተጠቀመ የሚገኝ በመሆኑ ነው፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ በዞኑ በተፈጠረው ግጭት ምክንያት በሕዝቡና በሌላው ሕብረተሰብ መካከል የጥላቻና የቂም በቀል መንፈስ ከመንገሱ አስቀድሞ የቤተክርስቲያን መሪዎች፣የአገር ሽማግሌዎች፣ ባለ ኃብቶች፣ ሴቶችና ተማሪዎች አንድ ላይ በመሆን በሕዝቡ መካከል የሽምግልናና የዕርቅ መድረክ በማዘጋጀት ዘላቂ መፍትሄ እንዲመጣ በአስቾካይ እንድትሠሩ እንጠይቃለን!!!

በአጠቃላይ የጌዴኦ ሕዝብ የኢህአዴግ/ህወኻት መንግስት 100% ፐርሰንት ደጋፊ ቢሆንም፣ ሕዝቡ ቀደምት አገሪቱን ሲያስተዳድሩ የነበሩት መንግስታት ያሳድሩበት የነበረው ዓይነት ጭቆናና በደል በኢህአዴግ የአስተዳደር ዘመንም እየተፈጸመበት ይገኛል፡፡ የጌዴኦ ሕዝብ እራሱን በራሱ እንዲያስተዳድር ዕድል የተሰጠው ቢመስልም፣ አከባቢውን እንዲያለማ መብት እንዳለው ቢገለጽም፣ከአገሪቱ ሃብት እኩል ተጠቃሚ እንደሚሆን እንዲሁም በአገሪቱ የፖለቲካ ስረዓት ውስጥ ዕኩል ተሳትፎ እንዲሚኖረው ቢነገርም፣ ባለፉት 25 ዓመታት ውስጥ የታየው ነገር የዚህ ሁሉ ተቃራኒ ሆኖ ተገኝቷል፡፡

ለዚህ ዋናው ምክንያት ኢህአዴግ/ህወኻት በጌዴኦ ዞን ጠንካራ አመራሮች በዘላቂነት ሕዝቡን እንዲመሩ ከማድረግ ይልቅ በየጊዜው ሹም ሽር እያካሄደ ሕዝቡን መሪ-አልባ እንዲሆን ማድረግ፣ ሕዝቡ የኢኮኖሚው ተጠቃሚ እንዳይሆን በሥውር የአርሶ አደሩን ማህበር በማዳከምና የኢኮኖሚ አቅሙን በማሽመድመድ፣ ከአጎራባች እና በዞኑ ከሚኖሩ የህብረተሰብ ከፍሎች ጋር ማጋጨት፣ ከመንግስት በኩል በፖለቲካውም ሆነ በፍትህ አስተዳደር ዘርፍ በቀላሉ መፍትሄ ሊያገኙ የሚችሉ ጉዳዮችን ሆን ብሎ በማዘግየት ወቅታዊ ችግሮች በሚፈጠሩበት ጊዜ ለመንግስት የፕሮፖጋንዳ መጠቀሚያ እንዲሆን የሚሰጠው ውሳኔና ያስከተለው መጥፎ ውጤት የጌዴኦ ሕዝብ የፈጠረው ችግር አድርጎ የማቅረብና የህዝቡን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ስነ-ልቦና ለማጥቃት እያካሄደ ከሚገኘው ከብዙ በጥቂቱ ይገለጻል፡፡

የጌዴኦ ሕዝብ በዞኑ ነዋሪ ከሆነው የሕብረተሰብ ክፍል (ጉራጌ፣ሲልጤ፣አማራ፣ ወላይታ፣ኦሮሞ፣ሲዳማ…ወዘተ) ጋር ምንም ዓይነት ችግር የለበትም፣ ሕብረተሰቡም እንደዚያው፡፡ በጌዴኦ ዞን ውስጥ ለተፈጠረው ቀውስ አገሪቱን በመምራት ላይ የሚገኘው የኢህአዴግ/ህወኻት መንግስት በዋናነት ተጠያቂ ነው!!!!!

ኢህአዴግ/ህወኻት የጌዴኦን ሕዝብ በሙስና፣በፍትህ እጦት፣በመልካም አስተዳደር ችግር፣በአንድ ብሔር የበላይነት በተፈጠረ የፖለቲካ ኪሳራ ምክንያት በተጨባጭ ቁልቁል እየወረደ ለሚገኘው የፖለቲካ ድርጅት የፕሮፖጋንዳ መሣሪያ መጠቀሚያነት የሚያደርገው ተግባር በአስቾካይ ይቁም!!!! ድርጊቱንም እናወግዛለን!!!!

ኢህአዴግ/ህወኻት በጌዴኦ ሕዝብ (ምሁራን፣የመንግስት ሠራተኞች፣መምህራን፣ መካከለኛ እና ከፍተኛ ባለኃብቶች እንዲሁም ወጣቶችና ተማሪዎች) ላይ እየተካሄደ የሚገኘው የጅምላ ግድያ፣እስር እና ኢ-ሠብዓዊ እርምጃ በአስቸኳይ ይቁም!!!!!!! ተግባሩንም አጥብቀን እንቃወማለን!!!!!!!

ፍትህና ነጻነት ለጌዴኦ ሕዝብ!!!!!! በውጭ የሚኖሩ የጌዴኦ ተወላጆች ኮሚዩኒቲ

12 December 2016 አሜሪካ /USA/

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s