የጣና በለስ ህገወጥ ሽያጭ፤ ንቀት ወይስ ማን አለብኝነት ? በእልፍኝ ሙሉ

 

በኢትዮጵያ ማህበረሰብ ከፍተኛ ዋጋ ከሚሰጣቸው ሃገራዊ የተፈጥሮ ሃብቶች መካከል መሬትና በውስጡም ሆነ በውጩ የሚይዛቸው አንጡራ ሃብቶች ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛሉ፡፡

የኢትዮጵያ ታሪክ በሰፊው እንደሚያሳየን የመሬት ባለቤትነት ጥያቄ የዜጎቿን ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም ፖለቲካዊ ግንኙነት በዋናነት ሲዘውር ቆይቷል፡፡ የመሬት ባለቤትነት ሃገሪቱ በውስብስብና ረጅም ሂደት ዓልፋ አሁን ላለችበትም የፖለቲካና የኢኮኖሚ ሁናቴ እንድትደርስ ፋኖ ጥያቄዎችም አንዱና ዋነኛው ነው፡፡ በተለይ በአብዛኛው ህብረተሰብ አርሶአደር በሆነበት አካባቢ የመሬት ባለቤትነትና መሬት የማግኘት መብት ለህዝቦች ህልውና አስፈላጊና ለፖለቲካዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ ተሳትፎ ደግሞ ብቸኛ አማራጭ መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል፡፡

ህወሃት የታላቋ ትግራይ ሪፐብሊክ የመመስረት ምኞቱ በታሪክ የተቀመጠና አሁንም ድረስ ‘ወርቃማ ሁለተኛው አማራጭ’ ተደርጎ ለማምለጫ ግዜ የተያዘ እንደሆነ በተለያየ ጊዜ የተገለፀ ነው፡፡ ይህን የመስፋፋት አላማ በህገመንግስት አስፍሮ ለማስፈፀም ለም የጎንደርና ወሎ ሰፊ መሬቶችን ወደ ትግራይ ክልል ውስጥ በሃይል ማስገባቱና አማራ ነዋረዎች ማንነት ላይ ጥቃት ከማርድረስም ባለፈ ውርደት እስራት መፈናቀልና እልቂት ማድረሱ ከዚሁ ጋር የሚያያዝ ሀቅ ነው ። በተመሳሳይ መልኩ በመላው ኢትዮጵያ ሃገሪቱን እንደ ነገዶች እስርቤት በመጠቀም በየ’ክልሎች’ ህወሃት ባለደረጃ ዜግነት አውጥቶ የኢትዮጵያን ህዝቦች በሃገራቸው ሁለተኛ ሶስተኛ አራተኛ ወዘተ ዜጋ አድርጓቸዋል፡፡ ከመሰረታዊ የመኖር መብት በተጣረሰ መልኩ ማንነታቸው ሳይጠየቅና ሳይሸማቀቁ በሁሉም ቦታ ሰርተውና ሃብት አፍርተው እንዳይኖሩ ከማድረግ አልፎ የነገድ ግጭት እሳቶችን ሲያፋፍም ቆይቷል፡፡ ለምና ሰፊ ለመስኖ የሚመቹ መሬቶች መውረር እንደፓለቲካና ኢኮኖሚ መሳሪያ የሚጠቀመው ህወሃት ላለፉት ሃያ አምስት አመታት ከሰሜን እስከ ደቡብ ከምስራቅ እስከምዕራብ ይህን አንጡራ ሃብት ለህወሃት ሰወች በመጀመሪያ ደረጃ ካከፋፈለ በኋላ ለተጫራች የውጭ ባለሃብቶች በርካሽ ቸብችቦ ወደ ህወሃት የኢኮኖሚ ኢምፓይር ገንዘቡን ያስተላልፋል፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ለአድር ባይ ካድሬወች ህሊና መግዣ የቀረውን ካቀራመተ በኋላ ምስኪኑን ህዝብ ለመፈናቀል ለውርደትና ለስደት ይዳርጋል፡፡

በአሁን ሰአት በአለም በርካሽና በስፍት ከ’ህዝባቸው’ ቀምተው የመሬት አንጡራ ሃብትን ለውጭ ኮርፖሬት ከሚቸበችቡት ሃላፊነት የጎደላቸው ስርዓቶች ውስጥ ህወሃት በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል፡፡ ይህ ትውልድን ለአዲስ-ቅኝ ተገዥነት የሚያረጋግጥ የህወሃት ሴራ ተስፋፍቶ በመቀጠል ግዙፍና ልዩ የሆነውን የጣና በለስ ሃገራዊ ፕሮጀክት ለቱርክ ኩባንያ በመቸብችብ እንደተለመደው የህወሃትን መሳፍንት ካዝና በውጭ ከረንሲ ሊደጉም እንደሆነ በገዥው መገናኛ ብዙሃን በመርዷችሁ ዝፈኑ በሚል ቃና ሰሞኑን ነግረውናል፡፡ ጣና በለስ ጣና ሃይቅን አካሎ የሚገኝ በሓይለስላሴ መንግስት እርሻን ያተኮረ ኢኮኖሚ በሚል ተጠንቶ በመንግስቱ ዘመን በከፊል ተግባር የተለወጠ ሃገራዊ ሃብትና ትልቁ ከአማራውም ህዝብ አልፎ የኢትዮጵያ እንጀራ እየተባለ የሚጠራ የህዝብ ሃብት ነው፡፡ ህወሃት በዚህ ፕሮጀክት ላይ አይኑን የጣለበት አማራን በመመዝበር ማዳከም የጀመረውና ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር ያሴረው ገና ጫካ በነበረበት ነው ተብሎ ይገመታል፡፡ ለዚህም ነው ከ400 በላይ ትራክተሮችና ብዙ ማሽኖችን አዲስ አበባን ከመቆጣጠሩ በፊት በቀትር ዝርፊያ ላይ ተሰማርቶ ወደ ወልቃይት ፀገዴ ሁመራ ሰቲት አላማጣ በመውሰድ የአማራን ገበሬ ማረሻውንም መሬቱንም ገፎ ለህወሃት የተቀቡ ቅፅበታዊ ባለሃብቶች ያለበሳቸው ፡፡ ይህም በህዝቦች መካከል የተጠመደ የግዜ ቦምብና ታሪክ የማይዘነጋው ጉዳይ ነው።

ህወሃት ይህ ቀዳሚ ቅሚያው አልበቃ ብሎት የውትድርና እና የደህንነት መስፍኖቹ በፈጠሩት የ’ኢንጅነሪንግ’ ማጭበርበሪያ (ስካም) ድርጅት ሜቴክ ጣና በለስን ያለማሉ በሚል ሰበብ የህዝብ ካዝናን በባንክ ብድር ስም ወደ ህወሃት የኢኮኖሚ ኢምፓየር በድጋሜ አራግፈዋል፡፡ ይህ የተደረገው ህዝባዊ መሰረት የነበራቸውና አቅም ያላቸውን የህብረተሰብ ተቆርቋሪ ባለሃብቶችን ከጨዋታ ውጭ በማድረግ እንደሆነ በተደጋጋሚ ተዘግቧል፡፡ አሁን በማን አለብኝነት ለሶስተኛ ጊዜ መሬቱን የህወሃት የኢኮኖሚ ድር ለደረሰበት የውጭ ምንዛሬ እጥረት መሸፈኛ ይሆነው ዘንድ ለቱርኩ አለማቀፋዊ በዴሳ ቡድን ግልፅ ባልሆነ አሻጥር ሊሸጥ እንደሆነ ተሰማ፡፡

የዚህ ከመቶ ሽዎች ሄክታር በላይ ስፋት ያለው ለምና ለመስኖ አመች የሆነ መሬት እንዲሁም በውስጡ የሚይዛቸው ኢኮ ሲስተም ለውጭ ባለሃብት መሸጥ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች ህይወት ላይ አሉታዊ አንድምታው ከፍተኛ መሆኑን የተለያዩ ጥናቶችና መላምቶች አሳይተዋል፡፡

በጨረፍታ ለመመልከት የሚከተሉትን መጥቀስ በቂ ነው፡፡

1. ብዙዎችን አርሶ አደሮች ከቀያቸውና ከእርሻ ቦታቸው ያልምንም ካሳ እያፈናቀለ ያለና ለከፋ ድህነት የሚዳርግ መሆኑ፡ ይህንንም እየተመለከቱ ያሉ ያይን እማኞች እየጮሁ የድረሱልኝ ጥሪ እያሰሙ ነው፡፡

2.ቢያንስ የአካባቢዉን ሁለት ትውልድ (ጀኔሬሽን) ያለርስት የሚያስቀር በህወሃት ተጋባዥነት የመጣ የእጀ አዙር ቅኝ መገዛትን የሚያስከትል መሆኑ፡ ከሌሎች ሃገር ልምድ ተነስተው የተፈጥሮ ሃብት ባለሙያወች ያሳስባሉ፡፡

3. የአካባቢውን የተፈጥሮ ሃብት በፍጥነት የሚሸረሽር ከመሆኑ ባሻገር ለመሬት ውሃ ብክለት የሚያጋልጥና የቱሪዝም መስቦች ድቀትና ጥፋት የሚያስከትል ነው ተብሎም ይታመናል፡፡

4.በአካባቢው ህዝብ ዘንድ አንድም ህጋዊ ተቀባይነትና ውክልና በሌለው የህውሃት ገዥዎች ምንም የህዝብ አስተያየት ሳይሰማበት ከመጋረጃ ጀርባ በድብቅ የተደረገ ዝርፊያ ስለሚሆን የማህበራዊ ደህንነትን የሚያሳጣ ብጥብጥም የሚያስከትል መሆኑን ባለሙያወች ያስጠነቅቃሉ፡፡

5.የጣና በለስ ተፋሰሰ ነዋሪወች ህልውና አደጋ ላይ የሚጥለው ይህ ፕሮጀክት ሽያጭ በጫካ ምንጠራ ዱር አራዊት ስደትና የአየር ፀባይ ለውጥ ያለው አሉታዊ ተፅእኖ የሚናቅ አይደለም፡፡

7. ከዚህ ሽያጭ ህዝቡ የሚያተርፈው ነገር ኢምንት ነው የሚሉት ባለሙያወች በዴሳ ኮርፖሬት ምርቱን ለአለማቀፍ ገብያና ትርፉን ለኮርፖሬት የሚያስገባ ሲሆን ርካሽና ቀቢፀ ተስፋ የህዝብ ጉልበት በከፍተኛው ይመዘብራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

8.ይህ የቱርክ ኮርፖሬት በሜካናይዝድ አስተራረስ የሚጠቀምና አነስተኛ የስራ እድል የሚፈጥር መሆኑ የታወቀ ሲሆን ህወሃትም እነዚህን አነስተኛ የጉልበት ስራወች በፖለቲካ ታማኞች እንደሚሞላ ይጠበቃል፡፡ የኮርፖሬቱ አላማ የምግብ ደህንነትን ማስጠበቅ ባለመሆኑና ህወሃትም ቅርጥፍጣፊ የውጭ ምንዛሬ ከታክስ ለማግኘት ስራው በንግድ ሰብሎች ላይ እንደሚያተኩር ቅድመ ፕላኖች ይጠቁማሉ፡፡ ይህም የአካባቢውን ሰወችና ሌሎችን ዜጎች በሃገራቸው የበይ ተመልካችና ተመፅዋችነትን ያመቻቻል፡፡

9. በተደጋጋሚ በኢትዮጵያም እንደታየው እንደዚህ ያሉ ከአካባቢው ህዝብ ጋር በተፃራሪ የሚቆሙ የጭቆና መሳሪያወች ቀጣይነታቸው አናሳ ነው የሚሉት ልምድ ያላቸው አማካሪዎች በግዜ ካልቆሙ ዋጋቸው ለህዝብም ሆነ ለኮርፖሬቱ የትየሌሌ ነው ሲሉ ያስጠነቅቃሉ፡፡

10. በአለማቀፍ ህግ ትልልቅ ኩባንያወች የሚንቀሳቀሱበትን ነዋሪ ህዝቦች እንዳይጎዱ የሚጠይቅ ስምምነት እንዳለ በጥናቶች ተጠቁሟል፡፡ ይህ ህግ ብዙ ግዜ ተፈፃሚነቱ ለህዝብ ተቆርቋሪ አስተዳደር መኖርንና የህዝብ ውክልናን ግምት ውስጥ ያስገባል የሚሉት የታዳጊ ሃገራትን የተፈጥሮ ሃብት አጥኝወች በኢትዮጵያ ሁለቱም አስፈላጊ ጥበቃወች አለመኖራቸው ችግሩን እጥፍ ድርብ ሊያደርገው ይችላል በማለት ፍርሃታቸውን ይገልፃሉ፡፡
ይህን ግዙፍ ስጋት ስር ሳይሰድና የህዝብ መሰረት ሳያጠፋ በእንጭጩ ለመቅጨት ለህዝብና ለአለም አቀፍ ተቋማት የችግሩን ምንነት ተፅኖውን ማስረዳት አንገብጋቢ ጉዳይ ነው፡፡ የህወሃት የአስቸዃይ ጊዜ አዋጅ የሚመራው መንግስት ጋር ውል የፈፀመው የቱርኩ በዴሳ ኮርፖሬት ቡድን ይህን አደጋ በሙሉ መነፀር በማየት ይህን አደገኛ ፕሮጀክን ከመግዛት እና አንጡራ ሃብታቸውን ከማፍሰስ እንዲቆጠቡ እስከወዲያኛውም ድረስ እንዲያቆሙት ግፊት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

ይህ ጫና ከተለያየ ቦታና በተለያዩ ዘዴወች ቢፈፀም ስኬታማ ይሆናል በማለት ሁሉም የሚመለከታቸው የኢትዮጵያ ህዝቦች የበኩላቸውን እንዲያደርጉና እንዲጮሁ ጥሪ እናደርጋለን፡፡ የዚህ አካል በሚሆኑት ጥረቶች እያንዳንዱ ዜጋ ፔትሽን በመፈረም ፤ ደብዳቤ ለበዴሳ በመፃፍ ፤ በማህበራዊ ገፆች ዘመቻ በመሳተፍ ቢያንስ ሃላፊነታቸውን ይወጣሉ ብለን ተስፋ እናደርጋለን። የሚመለከታቸውም ባለሙያወችና ህብረተሰቡን እንወክላለን የሚሉ ድርጅቶች ዘርፈ ብዙ አሉታዊ አንድምታውን በማጥናትና ለባለድርሻ አካላት በማስተዋወቅ የበኩላቸውን ከተወጡ ጥሩ ውጤት ለማግኘት ይረዳል፡፡ ኢንባሲዎች ፡ አለም አቀፍ የህግና ማህበራዊ ተቋሞች ፡ የመብት ተማጋቾች ፡ የብዙሃን መገናኛና የበዴሳ ባለስልጣናት ለዚህ ኢላማ ይሆናሉ፡፡

ይህን በጎንደር ጎጃምና ቤንሻንጉል ሰፊ ህዝብ የሚያፈናቅልና ለእጅ አዙር ቅኝ ግዛት የሚያጋልጥ ፕሮጀክት ማስቆም የሁሉም ህዝብ ሃላፊነት መሆኑን አስረግጠን እየተናገርን ይህን ለማስቀረት የምናካሂደውን አስቸዃይ ዘመቻ ትቀላቀሉ ዘንድ አደራ እንላለን!!

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s