የአማራ ድርጅቶች የተናጠል የፖለቲካ እንቅስቃሴ በተለይም ራሳቸውን የአንድነት ሃይል በሚሉ እና የአማራው ህዝብ መጀመርያ ራሱን ሊያድን ይገባዋል በማለት በአማራነት ላይ ያተኮረ ፖለቲካን ማራመድ በሚሹ መካከል ያለው ያለመደማማጥ እና በመርህ ደረጃ ያለመስማማት ችግር በጣም እንዳሳሰባቸው ብዙ የአማራ ተወላጆች እየገለፁ ይገኛሉ፡፡
በተለይም፤ የኦሮሞ ልሂቃን ልዩነታቸውን አጥብበው ወይም አቻችለው የነፃነት ቻርተር ለመንደፍ እየተጣደፉ በሚገኙበት ወቅት ከአማራ ልሂቃን ምንም አይነት የኢትዮጵያንም ሆነ የአማራን ህዝብ የወደፊት እጣፈንታ የሚገልፅ የፖለቲካ እቅድ ማዘጋጀት አለመቻል አስገራሚ ሆኖባናል ይላሉ፡፡ በአማራኒውስ በተካሄደው ሳይንትፊክ ያልሆነ ጥናት ከ64 በማህበራዊ ድህረ ገፆች ላይ የነቃ ተሳትፎ የሚያደርጉ የአማራ ለውጥ አራማጆች በፌስቡክ ገፆቻቸው ባለፉት 3 ቀናት ቢያንስ 54 የሚሆኑት ይህን የአመራር ክፍተትና ችግር እንደ ትልቅ እንቅፋት ገልየውታል፡፡